የአዲስ አበባ ከተማና የጀርመኗ በርሊን ቤሲርክ ሚቴ ከተማ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጀርመኗ በርሊን ቤሲርክ ሚቴ ከተማ ጋር በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሜቲ ታምራት እንደተናገሩት÷ስምምነቱ የሁለቱን ከተሞች ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ያጠናክራል፡፡
እንዲሁም በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡
ከበርሊን ቤሲርክ ሚቴ ከተማ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ የሚደረገውን ድጋፍ በቅርቡ በልደታ ክ/ ከተማ ለማስጀመር ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
የጀርመንዋ የበርሊን ቤሲርክ ሚቴ አስተዳደር ከንቲባ ስቴፋኒ ሬምሊንገር በበኩላቸው÷በከተማ ደረጃ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ በቀጣይ በበርሊን እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ለሚደረገው የእህትማማች ከተሞች ግንኙነት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በርሊን ቤሲርክ ሚቴ ከተማ በቅርቡ የሚያደርገው ድጋፍ በቀጣይ በሁለቱ ከተሞች መካከል ለሚኖረው የወዳጅነት ግንኙነት ትልቅ ማሳያ እንደሆነ መናገራቸውንም የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡