Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ወባን ለመከላከል የሚያግዝ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን የአልጋ አጎበር ተሰራጨ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያግዝ 1 ሚሊየን 400 ሺህ የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ መሰራጨቱን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታውቋል።

በተጨማሪም ከ14 ሺህ 900 ኪሎ ግራም በላይ ፀረ ወባ ኬሚካል በመቀሌ እና ወደ ወረዳዎች እየተከፋፈለ መሆኑን ቢሮው ገልጿል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከል ባለሙያ አቶ ጎይተኦም መሓሪ እንዳሉት÷ የአልጋ አጎበር የተሰራጨው ለወባ ተጋላጭ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች ለሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ነው።

ከፌደራል መንግስት ለክልሉ 1 ሚሊየን 500 ሺህ የአልጋ አጎበር መላኩንና ከዚህም ውስጥ እስካሁን 1 ሚሊየን 400 ሺህ አጎበር መሰራጨቱን አስታውቀዋል።

አጎበሩ ከሁለት ሚሊየን የሚበልጥ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ለወባ በሽታ አምጪ ትንኝ መራቢያ አመቺ ናቸው ተብለው የተለዩ ውሃ ያቆሩና ረግረጋማ ስፍራዎችን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የማጽዳት ስራም እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 14 ሺህ 918 ኪሎ ግራም ፀረ ወባ ኬሚካል ከፌደራል መንግስት ለክልሉ ተልኮ እየተከፋፈለ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው÷ ይህም በመቀሌና በ10 ወረዳዎች ውስጥ በቤቶች ላይ እንደሚረጭ አስረድተዋል።

በመቀሌ ሐወልቲ ከ/ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ብርሀን አረጋዊ በሰጡት አስተያየት÷ በጤና ባለሙያ እየታገዙ በአካባቢያቸው የወባ ትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን በማፅዳት ስራ ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.