የስራ ዕድል በመፍጠር ሂደት ውስጥ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን እንዲወጣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የሥራ፣ ኢንተርፕራዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከግል ባለሀብቶችና ከአምራችና ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር እየመከረ ነው።
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መንግስት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተለያዩ አማራጮች ጥረት ቢያደርግም ፍላጎቱን ማሟላት አልተቻለም ብለዋል።
በከተማው የሥራ አጥ ምጣኔውን ለመቀነስ ባሉት አማራጮች በዓመት ለ400 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ቢቻልም፤ ጤናማ ባልሆነ ፍልሰትና የውልደት ምጣኔ መጨመር ሳቢያ ፍላጎቱን ማርካት አለመቻሉንም አንስተዋል።
አሁን ላይ የመዲናዋ ስራ ፈላጊ ምጣኔ 22 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ጠቁመው÷ ችግሩን ለመቅረፍ የግሉ ዘርፍ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅበዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ በሥራ ዕድል ፈጠራው ንቁ ተሳታፊ በመሆን ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን ገልጸው÷ ይህንንም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በ2014 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ 421 ሺህ 850 የሥራ ዕድል መፈጠሩን እና ከዚህ ውስጥ÷ 278 ሺህ 464 ወይም 66 በመቶው በግሉ ዘርፍ የተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም በ2015 ዓ.ም ከተፈጠረው 339 ሺህ 697 የስራ ዕድል 216 ሺህ 363 ወይም 78 በመቶው የግሉ ዘርፍ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ ቅንጅታዊ አሰራሩን በማጠናከር ረገድ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።
በወንድሙ አዱኛ እና በሰለሞን ይታየው