Fana: At a Speed of Life!

የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ  ይሰራል – አቶ አሕመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የስራ እድል ፈጠራን እና የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ እንደሚሰራ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

አቶ አሕመድ ሺዴ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2016 ረቂቅ በጀት ምክክር ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያም ለአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የበጀት ድልድል የሚደረገው የመንግስት የትኩረት አቅጣጫን፣ የተቋማቱን የማስፈጸም አቅም በማየት እንዲሁም መስሪያ ቤቶቹ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተመደበው በጀት በተወሰነ ደረጃ አፈጻጸምን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ጠቅሰው÷ ወጪ ቅነሳ ሊደረግባቸው የሚገቡ የወጪ መደቦችን በአግባቡ የፈተሸና ተገቢውን ማስተካከያ የተደረገበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ተቋማት በአሰራር ጭምር መስራት ስላለባቸው የበጀት ድልድሉ ይህንንም መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ተቋማት በአነስተኛ አደረጃጀት የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ አሕመድ ሺዴ፥ በሚቀጥለው አመት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ አላማም በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት እንዳይሰፋ መቆጣጠር መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም እድገትን ማስቀጠልና የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ሁኔታን መፍጠር መቻል የማክሮ ኢኮኖሚ አላማዎች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

የስራ እድል ፈጠራ ላይ መስራት እና የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ እንደሚሰራ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የቀረበው በጀት ትልቁ አላማ የዋጋ ንረት እንዳይሰፋ ማድረግ፣ በበጀት የሚሰሩ የልማት ስራዎችንም ማስቀጠልና የበጀት ጉድለት እንዳይሰፋ ማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለመጨረስ የሚያስፈልገው በጀት በጣም ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ አሕመድ ሺዴ÷የበጀት ድልድሉም እነዚህን ሁኔታዎች በማጣጣም የተዘጋጀ ነው ብለዋ፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.