Fana: At a Speed of Life!

ቱርክ እና ግብፅ ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን ሊያድሱ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ እና ግብፅ ሻክሮ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ሊያድሱ መስማማታቸው ተገለጸ፡፡

ሀገራቱ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ካካሄዱ በኋላ በየሀገራቱ የየራሳቸውን አምባሳደር መሠየማቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በዛሬው ዕለት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለቱን ሀገራት ስምምነት የሚያንጸባርቅ መግለጫ አውጥቷል።

በዚህም መሠረት ቱርክ ሳሊህ ሙትሉ ሴን በግብፅ የሀገሪቷ አምባሳደር ሆነው እንዲሠሩ የሠየመች ሲሆን፥ ግብፅ በበኩሏ አምር ኤልሃማሚን በቱርክ ሀገሪቷን እንዲወክሉ በአምባሳደርነት መሾሟን አስታውቃለች፡፡

የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሻከረበት አንስተው ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር ውሳኔ ላይ የደረሱት የየሀገራቱ ፕሬዚዳንቶች ከመከሩ በኋላ መሆኑን የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመረጃው ጠቁሟል፡፡

ውሳኔው የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ቀድሞው ለመመለስ ያለመ ነውም ተብሏል፡፡

ቀደም ሲል ሀገራቱ በባላንጣነት የሚተያዩ እና መሪዎቻቸውም እርስ በእርስ በአደባባይ የሚወራረፉ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል።

ሀገራቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባላንጠነታቸውን ወደ ጎን ብለው በሚኒስትሮች ደረጃ የወዳጅነት መልዕክቶችንና በሀገራቱ መካከል ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር የሚያስችሉ ድርድሮችን ሲያካሂዱ መቆየታቸውም ተነግሯል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.