Fana: At a Speed of Life!

አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ የ411 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም /አይ ኤም ኤፍ/ ለኢትዮጵያ የ411 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ድጋፍ አፀደቀ።

የተቋሙ ቦርድ ያፀደቀው ድጋፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ነው ተብሏል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ቦርድ በድርጅቱ አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ አሠራር ማእቀፍ አማካኝነት ነው ድጋፉን ያደረገው።

አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት መከታተሉን እንደቀጠለ በመግለፅም እንደ አስፈላጊነቱ የፖሊሲ ምክርና የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑ ነው ያረጋገጠው።

ተቋሙ ኢትዮጵያ በዚህ ቫይረስ ምክንያት ተጋላጭ እና ታዳጊ የሆኑ ሀገራት የብድር ክፍያ እርፍታ እንዲያገኙ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 13 ቀን 2020 ያሳለፈው ውሳኔም ተጠቃሚ እንደምትሆንም አስታውቋል።

ውሳኔውን ተከትሎ የተቋሙ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ታኦ ዣንግ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዋ ውስጥ የግሉን ዘርፍ ሚና ለማሳደግ ከተቋሙ በወሰደቸው የገንዘብ ፈንድ መልካም ለውጥ ማሳየቷን ተናግረዋል።

የሀገሪቱ መንግስት ይህን ለውጥ ለማስቀጠል ፍላጎቱ ቢኖረውም ኮቪድ-19 ግን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ተፅእኖ በማሳረፍ አስቸኳይ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያስፈልጋት አድርጓል ነው ያሉት።

መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በፍጥነት እርምጃዎች መውሰዱን አንስተዋል።

በዚህ ጊዜ ጊዜያዊ የበጀት ጉድለት ቢኖር ተገቢ መሆኑን በማንሳትም አሁን ላይ መንግስት በጤና አገልግሎት ማስፋፋት እና የምግብ ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች አስቸካይ እርዳታዎች ማቅረብ ላይ ማተኮሩን ገልፀዋል።

ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የተቋሙ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂየቫን ብቃት ለተሞላበት አመራራቸው እና የኮቪድ-19ን ቀውስ በምንመክትበት በዚህ ወቅት ከጎናችን በመቆማቸው ምስጋና አቅርባለሁ ብለዋል።

እንዲሁም ድጋፉ ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚያስፈልጋትን የገንዘብ መጠን መቶ በመቶ የሚሸፍን ነው ብለዋል።

የአይ ኤም ኤፍ ቦርድ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብሩን ለመደገፍ ባለፈው ኅዳር ድጋፍ ማድረጉም ይታወሳል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.