Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የዓለም የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ዛሬ እየተከበረ ያለውን የዓለም የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
 
እንኳን ለዓለም የሠራተኞች ቀን በሰላም አደረሳችሁ!
 
ውድ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ሕዝቦች፤
 
በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን (ሜይ አንድ) የሚከበረው
የዓለም ሠራተኞችን ሕይወት የቀየሩ የሠራተኞች ትግሎች የሚታወሱበት ቀን ነው፡፡ ሠራተኛው የኀብረተሰብ ክፍል ለሚሰጠው አገልግሎት ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲከፈለው፣ ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ እንዲኖር፣ በሥራ አካባቢው የሥራ ዋስትናና ደኅንነቱ እንዲጠበቅ፣ ሰብአዊ መብቱ እንዲረጋገጥ፣ የመደራጀት መብቱ እንዲከበር፣ የተደረጉ አያሌ ትግሎች አሉ፡፡ በሀገራችን ምንም እንኳን የሠራተኛው ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ለመብትና ለነጻነቱ ያደረገውና ዛሬም የሚያደርገው ትግል ግን ከቁጥሩ በላይ ታሪክ የቀየረ ነው፡፡
 
አሁን ያለንበት ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር ውስጥ እንደ ጥንቱ ዘመን፣ ‹ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች› ተብሎ ብቻ የሚፎከርበት እንዳይደለ ሁላችንም እናውቃለን ፡፡ ግን ደግሞ ዓለም ከሠራተኛ ልጆቿ ውጭ ምንም ናት፡፡ የሀገራችን ጉዞ አምራች ኢንዱስትሪውን ወደ ማስፋፋት የሚደረግ በመሆኑ ስለ ሠራተኛው ማኅበረሰብ ስንነጋገር ስለ ቀጣይዋ ኢትዮጵያ እየተነጋገርን እንደሆነ እናምናለን፡፡ ስለ ሠራተኛው የኑሮ፣ የሥራና የጤና ሁኔታ ስናስብ፣ የሠራተኛውን መብቶችና ጥቅሞች ስናስብ፣ የሠራተኛውን የሥራ ዋስትናና ዕድገት ስናስብ፤ ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ እያሰብን ነው፡፡
 
በመሆኑም በሠራተኛው እና በአሠሪው መካከል የሚኖረው ግንኙነት የነገዋን ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረገ ግንኙነት እንዲሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡ ትብብር እና መደጋገፍን መሠረት ያደረገ፣ በሕግና በሞራል የሚመራ፣ የሠራተኛውን መብት ከሀገሪቱ ዕድገትና ከኢንዱስትሪው ሰላም ጋር ያጣጣመ መሆን ይኖርበታል፡፡ የሠራተኞች መብት የማይከበርበት ኢንዱስትሪ ሕይወት አልባ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢንዱስትሪያቸው ሰላምና ትርፋማ እንዲሆን የማይሠሩ ሠራተኞችም ራሳቸውን በራሳቸው የሚያጠፉ ሠራተኞች ናቸው፡፡
 
ሠራተኞችና አሠሪዎች ለአንድ ሀገራዊ ግብ የሚሠሩ ሁለት አካላት ናቸው፡፡ ተደጋግፈውና ተግባብተው፣ተደራድረውና ተስማምተው እንጂ ተቃርነውና ተጋጭተው ውጤታማ አይሆኑም፡፡ ተባባሪነት እንጂ ባላንጣነት አያዋጣቸውም፡፡ በጥናትና በድፍረት ወደ ኢንዱስትሪው የሚገቡ፣ ችግሮችን ተቋቁመው የሚያልፉ፣ ትውልድ ተሻጋሪ ማምረቻዎችን የሚተክሉ ባለ ሀብቶችን እንፈልጋለን፡፡ የእነዚህን ባለ ሀብቶች ራእይ ወደ ተግባር የሚለውጡ፣ በሞያና በዲሲፕሊን የታነጹ ሠራተኞችንም እንፈልጋለን፡፡ የነገው ብልጽግናችን የሁለቱ ድምር ውጤት ነው፡፡
 
አሠሪዎች የሠራተኞችን መብት ማክበር ያለባቸው፣ ጥቅሞቻቸውን መጠበቅ ያለባቸው፣ መደራጀታቸውን መደገፍ ያለባቸው ለራሳቸው ሲሉ ጭምር ነው፡፡ ክብሩና ጥቅሙ ያልተከበረለት ሠራተኛ ምርታማ፣ ውጤታማና ጤናማ አይሆንም፡፡ ሠራተኞችም የኢንዱስትሪውን ትርፋማነት፣ደኅንነት፣ ወጭ ቆጣቢነት፣ ሰላምና ዘላቂነት ማስጠበቅ ያለባቸው የመኖራቸው ምክንያት፣ የሀገራቸውም የዕድገቷ መሠረት ስለሆነ ነው፡፡ የዘንድሮው የዓለም የሠራተኞች ቀን በዚህ መንፈስ ሊከበር የሚገባው ነው፡፡
 
የዘንድሮው የሠራተኞች ቀን የሚከበረው በኮሮና ወረርሽኝ ውስጥ በሆነች ዓለም ነው፡፡ ወረርሽኙ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የጤና፣ የማኅበራዊ ደኅንነት፣ ወዘተ. ፈተና ሆኖ መጥቷል፡፡ ለሠራተኞች ደግሞ ከባድ የሆነ የሥራ ዋስትና ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በተለይም በሀገራችን በእግሩ መሄድ የጀመረውን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ወደ ዳዴ እንዳይመልሰው ማድረግ ይገባናል፡፡ በከፍተኛ ጥበብ፣ ኃላፊነትና ቁርጠኝነት መሥራት ያለብን ጊዜ ነው፡፡
 
መንግሥት በአንድ በኩል የሠራተኞች የሥራ ዋስትና እንዲጠበቅ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አምራች ኢንዱስትሪው በወረርሽ ተጽዕኖ ሳይሰበር እንዲቀጥል ለማድረግ አስፈላጊ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው፡፡ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆንም ተፈላጊውን ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሠራተኛው በአንድ ጎን የገጠመንን ፈተና ሊያካክስ በሚችል መልኩ የበለጠ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ ጎን ደግሞ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሌሎችን ከበሽታው በመጠበቅ የበሽታውን ተጽዕኖና እድሜ ለመቀነስ መጣር ይኖርበታል፡፡
 
ሥራችንን በቤታችን ወይም ተገቢውን ጥንቃቄ አድርገን በሥራ ቦታችን ማከናወን አለብን እንጂ ለአፍታም መታከት አይገባንም፡፡ ወቅቱን የማረፊያ ሳይሆን አብዝቶ የመሥሪያና፣ ብዙ የማትረፊያ አድርጎ መውሰድ ይገባል፡፡ ወቅቱ ብክነትን በመከላከልና ወጭን በመቆጠብ የምንሠራበት ወቅት ነው፡፡ አዳዲስ ፈጠራዎችን ተጠቅሞ ለገጠመን ፈተና መፍትሔ በማፈላለግ፣ ከፍተኛ ወጭ የምናወጣባቸውን የውጭ ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ያለንን ዕውቀትና ሀብት ከሌሎች ጋር በመካፈል፣ ይሄንን ወቅት ተጋፍጠን ልናሸንፈው ይገባል፡፡
 
ከፊታችን የተቀመጠው አማራጭ ሁለት ነው፡፡ ወይ ኮሮና በእኛ ላይ ያልፋል፤ አለያም እኛ በኮሮና ላይ እናልፋለን፡፡ ኮሮና ሲያልፍ ኮሮና ካመጣብን ችግር ይልቅ ችግሩን ለመቋቋም ስንል በፈጠርናቸው መፍትሔዎች፣ባፈለቅናቸው ሐሳቦች፣ በከፍተኛ ሁኔታ ባመረትናቸው ምርቶች፣ በየአካባቢያችን በፈጠርናቸው ትብብሮች፣ ከጊዜ፣ ከዕውቀትና ከገንዘብ በከፈልናቸው መሥዋዕትነቶች የምናስታውሰው ከሆነ፤ እኛ በኮሮና ላይ ድል አድርገን አልፈናል ማለት ነው፡፡ ኮሮና ሲያልፍ አብሮን የሚቀረው ያጋጠመን ኪሣራ፣ ያለቀብን ወገን፣ የፈጠርነው ዝርክርክነት፣ ያልሠራነው ሥራ፣ ያልወሰንነው ውሳኔ፣ ያልከፈልነው መሥዋዕትነት ከሆነ፣ ኮሮና በእኛ ላይ አድቅቆን አልፏል ማለት ነው፡፡
 
የኢትዮጵያ ሠራተኞች እኛ በኮሮና ላይ እንድናልፍ እንጂ፣ ኮሮና በእኛ ላይ እንዲያልፍ እንደማይፈቅዱ ሙሉ እምነቴ የጸና ነው፡፡ ለዚህም ከነገው ጊዜ ተበድራችሁ ዛሬ የምትችሉትን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡
መልካም በዓል!
 
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዚያ 23 ቀን 2012 ዓ.ም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.