የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የ7 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን የ7 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ።
የድጋፍ ስምምነቱ የተደረገው የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በተገኙበት የኢትዮጵያ የብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተፈራርመዋል።
ህብረቱ ድጋፉን ያደረገው ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው ብሔራዊ ምክክር በውጤት እንዲጠናቀቅ በማለም ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው በስምምነቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የተደረገው ድጋፍ ኮሚሽኑ በቀጣይ ለሚሰራቸው ስራዎች ያግዛል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ወደፊት እንዲጓዝ ሌሎች የአውሮፓ አባል ሀገራት ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ ይገባልም ነው ያሉት፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፥ ኮሚሽኑ አስፈላጊ ስራዎችን አጠናቆ ምክክር ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የኮሚሽኑ ስራ የተቃና እንዲሆን ከመንግስትና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው÷ የተደረገው ድጋፍ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮናልድ ኮቢያ፥ የአውሮፓ ህብረት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በአንክሮ ሲመለከተው የነበረና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሚያግዝ መሆኑን በመገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።
ስምምነቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በተገኙበት ነው የተፈረመው።
በቅድስት አባተ