ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአማራ እና በትግራይ መካከል ያሉ የቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች በስክነት እንዲታዩ ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፊዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአማራ እና በትግራይ ክልል ያሉ የቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች በስክነት እንዲታዩ ጠየቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው አስታውሰዋል፡፡
ይህን ጉዳይ በተመለከተም በተለይም የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ በሰከነ መንገድ እንዲያዩት እመክራለሁ ብለዋል፡፡
በመሬት ምክንያት መባላት እና መገዳደል እንደማያስፈልግም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
መሬት የጸብ ምንጭ መሆን የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሕዝቦች ተወያይተው፣ ተመካክረው፤ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሳይሆን ጊዜ ወስደው በሰከነ መንገድ በየትኛው ክልል መኖር እንደሚችሉ መወሰን ይችላሉ ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው