የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአርባምንጭ ከተማ ያስገነባውን ካምፕ አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአርባምንጭ ከተማ ከ180 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን የደቡብ ሬጅመንት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ አስመረቀ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ካምፑን በይፋ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በከፍተኛ ደረጃ በማደራጀትና ለግዳጅ ማብቃት አንዱ የሪፎርም ስራ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፤ በተመረጡ የወታደራዊ ፖሊስ ስትራቴጂክ ቦታዎች ላይ ሰፋፊ የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ዋናው የፖሊስ ሥራ ከህዝብ ጋር በመቀናጀት የሚሰራ በመሆኑ የፌደራል እና የክልል ፖሊስ አመራርና አባላት የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም የህብረተሰቡን ባህልና እሴት መጠቀም እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የጋሞ ኅብረተሰብ ባህልና እሴትን በአብነት አንስተዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳደር አቶ ትቆ ትላንቴ በበኩላቸው በአርባምንጭ ከተማ የተገነባው ካምፕ የአካባቢውን ሰላም ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ከለውጥ ማግስት ጀምሮ የፖሊስን ተቋም ለማዘመንና አገልግሎቱን ለማስፋትና ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ ክልሎች ለሠራዊቱ አባላት የሚውል ካምፕ ተገንብተው ለአገልግሎት እየበቁ እንደሆነ የተቋሙ የሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ ፊጣ ማመልከታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።