Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ ሲጀመር ለፋይናንስ ዘርፉ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል- የኢሲኤ ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ገበያ ሲጀመር ለፋይናንስ ዘርፉ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔትሮ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ ዓለም አቀፍ የባንኮች ዘርፍና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ውይይቱ ”ለኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ግብይት ለካፒታል ገበያ የኢኮ-ሲስተም የአቅም ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተካሄደው፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔትሮ÷መድረኩ ለኢትዮጵያ የሰነደ መዋለ -ንዋይ ምስረታ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ- ንዋይ ገበያ መጀመር ትልቅ ትርጉም ያለውና ለፋይናንስ ዘርፉም አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልፀዋል።

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷በቀጣዩ ዓመት የሰነደ መዋዕለ-ንዋይ ግብይትን እውን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የካፒታል ገበያ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ በመደገፍ በዘላቂ የልማት ግብ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው÷የሰነደ መዋዕለ-ንዋይም ከዚሁ ጎን ለጎን የሚተገበር ይሆናል ብለዋል።

የገበያውን ግንዛቤ በማሳደግ፣ የኢንቨስተሩን ፍላጎት በመጨመር፣ የገበያ ሳቢነት በመፍጠር በኢኮኖሚው ውስጥ የላቀ ሚና እንደሚኖረው መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.