Fana: At a Speed of Life!

የቡናና ሻይ ባለስልጣን ሰራተኞች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ኬላዎች ላይ የሚሠሩ 15 የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሰራተኞች

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለፀ።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በጋራ በመተባበር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጅማ፣ በወለጋ፣ በደሴ፣ በቱሉ ዲምቱ፣ በጎጃም፣ በአቃቂ፣ በቢሾፍቱ፣ በቡሌ ሆራ፣ በሀገረማሪያም በር እና በሌሎች ኬላዎች በተደረገ ኦፕሬሽን በቁጥጥር መዋላቸው ነው የተገለጸው፡፡

በኦፕሬሽኑም የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ እና ብር እንዲሁም ሕገ-ወጥ ሽጉጦችና ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከመሰል ጥይቶች ጋር መያዛቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ኬላዎች ላይ ተመድበው በሚሠሩበት ወቅት በተቋሙ የተሠጣቸውን ኃለፊነት ወደ ጎን በመተው ከአንዳንድ ላኪ ነጋዴዎች ጋር ኔትዎርክ ፈጥረው ገንዘብ በመቀበል ከአሠራር ሥርዓት ውጭ ሲሲሰሩ እንደነበር የምርመራ ቡድኑ ገልጿል።

ግለሰቦቹ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ያለበትን ቡና በሕገ-ወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ እንዲሸጥ በማድረግ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ በማሳጣት በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።

ኀብረተሰቡ ለፀጥታ አካላቱ ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ላለው ትብብር ምስጋና ያቀረበው ፌዴራል ፖሊስ በቀጣይ ለሚካሄዱ ኦፕሬሽኖችም ተሳትፎው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.