Fana: At a Speed of Life!

ጀርመን በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር  ስቴፈን አወር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ሀገራቸው በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ እርዳታ የምታደርገውን ድጋፍ በእጥፍ አሳድጋለች፡፡

ጀርመን የሰሜን ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በግጭት የተጎዱ አካባቢዎቸን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍም አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ለሰላም ስምምነቱ ትግበራ እንዲሁም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና ለሽግግር ፍትሕ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ሰላም እና መረጋጋት መምጣቷን የገለጹት አምባሳደሩ÷ሀገራቸው ግጭቱን ለማቆም ለወሰኑ አካላት እውቅና ትሰጣለች ብለዋል፡፡

ጀርመን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ እና በሁሉም ዘርፎች የተጀመረው ለውጥ እንዲጠናከር  ድጋፏን  ታጠናክራለች ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት መጠናከር ከምታበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር የአህጉሪቱን አንድነት ለመፍጠር ከፍተኛ እጥረት እያደረገች ነው ብለዋል ፡፡

አምባሳደር ስቴፈን አወር ÷ ኢትዮጵያ በቀጣይ የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማዕከል የመሆን ትልቅ እድል አላት ሲሉም አውስተዋል፡፡

 

በዮናታን ዮሴፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.