Fana: At a Speed of Life!

በኮቪድ-19 ምክንያት በሰራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጪ የስራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ምክንያት በሠራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የሥራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ለ45ኛ ጊዜና በዓለም ለ131ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን (ሜይዴይ) አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የስራ ቦታና ሰራተኛው ለወረርሽኙ ያለውን ከፍተኛ ተጋላጭነት በተመለከተ በመልዕክታቸው ዳሰዋል።

የዘንድሮው ሜይዴይ የሚከበረው የኮሮና ቫይረስ በሚያስደነግጥ ፍጥነት ዓለምን በወረረበትና በሠው ልጅ ላይ አደጋ በደቀነበት ጊዜ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል ሃገሮች ጥረት እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ የሚደረገው ትግል የተለያየ መስዋዕትነት እየጠየቀ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያም የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ ”በመንግስት፣ በአሠሪና ሠራተኛ አካላት ምክክር የወጣው “የኮቪድ-19 የሥራ ቦታ ምላሽ የሦስትዮሽ ኘሮቶኮል” እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሥራ ቦታ ላይ የጣለውን ኃላፊነት መተግበር ያስፈልጋል” ብለዋል።

በሠራተኛው ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የሥራ ዋስትና እጦት እንዳይደርስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረው፥ ተባብሮና ተደጋግፎ የመሻገር ጉዟችን ቀዳሚ ትኩረት ነው ብለዋል፡፡

ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ደህንነት መቆምንና በአንድነት መሰለፍን የሚጠይቅበት ጊዜ በመሆኑ ለሰራተኛው መብት መከበር በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል ሰራተኛው ራሱን እየጠበቀና ሌላውን እየታደገ በአሸናፊነት ለመሻገር በተደራጀና በተቀናጀ አቅም አንድ ላይ መስራት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ወረርሽኙን የመከላከያ መንገዶችንና የጥንቃቄ ደረጃዎችን በመከተል ሠራተኛው ከወረርሽኝ እንዲጠበቅ ማድረግ ይገባል።

ሜይዴይ የዓለም ላብ አደሮች ያለፉበትን የትግል ውጣውረድና የጨበጡትን ድል የሚያስቡበትና መጪውን ዘመን አሻግረው የሚያስተውሉበት ቀን መሆኑን አውስተዋል።

የዓለም ሠራተኞች አካልና የትግል አጋር የሆነው የኢትዮጵያ ሠራተኛም ከዓለም አቀፍ የላብ አደሮች የትግል ጉዞ የተለየ ታሪክ እንደሌለው ያስታወሱት ዶክተር ኤርጎጌ፤ ”በኢትዮጵያ የማምረቻው ዘርፍ ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከበር ያደረጉት መራር ትግል በደማቅ ቀለም ተፅፏል” ብለዋል።

በተደረገው ትግልም ሠራተኛው በሥራ ቦታ ክብርና ደህንነቱ፣ መብትና ጥቅሙ እንዲከበር መንገድ የከፈተ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ሜይዴይ ሲከበር ለሰራተኛው መብት የታገሉትን ሠራተኞችና የሠራተኛ መሪዎች ክብር እንደሚገባቸው አንስተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታትም ተመሳሳይ ገድል እንዲፈጽሙ ጠይቀዋል።

”ሠራተኛው ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተጠብቆ የላቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን እየታገለ የከፈለው መስዋትነት ሜይዴይ በተከበረ ቁጥር ሲዘከር ይኖራል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.