የመጀመሪያው የወባ ክትባት ለአፍሪካ ሀገራት ሊሰራጭ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 30 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የጤና ድርጅት የመጀመሪያውን የወባ ክትባት በቅርቡ በአፍሪካ ሀገራት እንደሚያሰራጭ አስታወቀ።
ድርጅቱ እንዳስታወቀው በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ውስጥ 18 ሚሊየን የወባ ክትባቶች በ12 የአፍሪካ ሀገራት ይሰራጫሉ።
‘ሞስኪውሪክስ’ የተሰኘው ክትባት ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ በጋና፣ ኬንያ እና ማላዊ በሙከራ ደረጃ ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ህጻናት መሰጠቱን ዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት እና የተመድ የህጻናት ፈንድ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ቤኒን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቡሩንዲ፣ ካሜሩን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ኒጀር፣ ሴራሊዮን እና ኡጋንዳ ደግሞ ክትባቱን በቅርቡ ይረከባሉ መባሉን አር ቲ በዘገባው አመላክቷል።
ይህን ክትባት ለመውሰድ እስካሁን 28 ሀገራት ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፥ የመጀመሪያው ክትባት በተያዘው የፈረንጆቹ አመት የመጨረሻ ሩብ አመት ለሀገራቱ ይደርሳል ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2021 ብቻ በአፍሪካ ከአምስት አመት በታች የሆኑ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ህጻናት በወባ በሽታ ለህልፈት መዳረጋቸውን የዓለም ጤና ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርጎ አር ቲ አስነብቧል።
ክትባቱ በብሪታንያ ዓለም አቀፍ የፋርማሲዩቲካል ኩባንያ የተመረተ መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል።