የመርማሪ ቦርዱ አባላት የከተማ አስተዳደሩ ኮቪድ19ን ለመከላከልና የገቢ ምንጭ የሌላቸውን ነዋሪዎች ለመደገፍ ያሰባሰባቸውን ንብረቶች ጎበኙ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ አባላት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮቪድ19ን ለመከላከልና የገቢ ምንጭ የሌላቸውን ነዋሪዎች ለመደገፍ ያሰባሰባቸውን ንብረቶች ጎብኝተዋል።
የከተማዋ የወጣቶችና የበጎ ፈቃደኞች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ በከተማዋ ቫይረሱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በማህበራት የተደራጁና በግለሰብ ደረጃ 3 ሺህ 884 ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ስራ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አድራጊ ወጣቶችን ገንዘብ ጨምሮ ሀብት የማሰባሰብ፣ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የመስጠትና እጅ የማስታጠብ፣ ደም የመለገስ እንዲሁም የተሰበሰበውን ሀብት በመጋዘኖች የማከማቸት ስራ እየሰሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ከዚህ ውስጥ ያልተፈጨ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ፍርኖ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ፍራሽና ብርድ ልብሶች፣ ፓስታና ማካሮኒ፣ የንፅህና መጠበቂያዎች በዋነኛነት እንደሚገኙበት ገልፀዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ አባላት በበኩላቸው የቫይረሱ ወረርሽኝ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የከተማ አስተዳደሩ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አድንቀዋል።
ገንዘብን ጨምሮ ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰቡት ሀብቶች ለብክነት እንዳይጋለጡ እና ክፍፍሉም ከአድሎ የፀዳ እንዲሆን ተገቢውን ክትትል ማድረግ ይገባል ማለታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።