ስኳርን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ማር ነው በማለት ሲያዘጋጁ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስኳርን ከተለያዩ ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ማር ነው በማለት ሲያዘጋጁ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን ሲያከናውኑ የነበረው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው በተለምዶ ፋንታ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው።
በአምስት በርሜል ሲዘጋጅ የነበረ ማር እና ተዘጋጅቶ ለገበያ ሊውል የነበረ ዘጠኝ ማዳበሪያ ማር መሰል ነገር ተይዟል።
ተጠርጣሪዎቹ ማሩን ለማዘጋጀት ምንነቱ ያልታወቀ ኬሚካል፣ ቀይ እና ነጭ ዱቄት ፓውደር እንዲሁም ስኳር ተጠቅመዋል ነው የተባለው።
አሁን ላይም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የምርመራ መዝገብ በማደራጀት እየተጣራ መሆኑ ነው የተገለጸው።
ሁሉም ሰው በየአካባቢው በጥርጣሬ እና ትኩረት በመስጠት በማንኛውም ጊዜ ከፖሊስ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ህገ ወጥ ተግባራትን ሊከላከል ይገባል መባሉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።