ኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው 521 ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው 521 ሰዎች ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙት ሰዎች ከመጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ናቸው ተብሏል።
ከተጠቀሰው እለት ጀምሮ 2 ሺህ 516 ሰዎች ተለይተው ክትትል ሲደረግላቸው የቆየ ሲሆን፥ 1 ሺህ 953ቱ ክትትላቸውን አጠናቀው ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው ቀሪዎቹ 521 ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል ነው የተባለው።
በኢትዮጵያ እስካሁን ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 42ቱ በቅርብ ንክኪ የነበራቸው ሰዎች መሆናቸው ተረጋግጧል።
በአጠቃላይ ህብረተሰቡ በሽታው በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ መልዕክቶችን እና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።
ህብረተሰቡ የቫይረሱን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎች በሚያገኝበት ወቅትም በተዘረጉ የነጻ የስልክ መስመሮች በመደወል እንዲያሳውቅና የቫይረሱን ስርጭት በመቆጣጠር በኩል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ መቅረቡን ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።