ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከ300 በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የማስፈጠር ፕሮግራም አካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ከ300 በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ የማጋራት (የማስፈጠር) ፕሮግራም አካሄደ።
ሚኒስቴሩ የረመዳን ፆመን በማስመልክት ነው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ቤተሰቦችን ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ኤምባሲ ጋር በመተባባር ማዕድ የማጋራት ፕሮግራሙን ያካሄደው።
በፕሮግራሙ ላይ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ እንደገለፁት የማህበራዊ ሃላፊነት በሁሉም ተቋማት እንዲጎለብት በማድረግ ባለሃብቶች መሰል ድጋፎችን ማድረግ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዋነኛ ሃላፊነት አድርገው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።
ህብረተሰቡም ጎረቤቱን በማስታወስና በመደገፍ የቆየ እሴቱን ማጎልበት እንደሚኖርበት ጠቅሰው፥ ይህን ማድረግ ከተቻለም አስቸጋሪውን ወቅት ማንንም የከፋ ችግር ላይ ሳይጥል መሻገር ይቻላል ብለዋል።
በዕለቱ ለህብረተሰቡ ከታደሉት ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች መካከል ዘይት፣ ሩዝ፣ ዱቄት፣ ቴምር እንዲሁም ተይዘው የሚወሰዱ ምግቦች እንደሚገኙበት ከሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።