Fana: At a Speed of Life!

የአፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የክረምት ወራት ሥራዎች ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የክረምት ወራት ሥራዎች ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በአፋር ክልል የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፣ በግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ መሐመድ የአፋር ክልል በክረምት ወራት የሚከናወኑ ሥራዎችን ዕቅድ አቅርበዋል፡፡

ውይይቱ በአፋር ክልል በተገኙ ውጤቶች፣ ተግዳሮቶችና ቀጣይ ትኩረቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልሉ የተከናወኑ የበጎ ፍቃድ ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ ፣ የሌማት ትሩፋት ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎች እና የተገኙ ውጤቶች በውይይቱ ተዳሰዋል፡፡

በተመሳሳይ በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ የተመራ ልዑክ በክረምት በሚከናወኑ ዘርፈ-ብዙ የልማት ሥራዎች ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።

በመድረኩም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የልማት ግቦችን ለማሳካት በተደረገ ርብርብ እየተመዘገቡ ያሉ አመርቂ ውጤቶችን ማስቀጠል እና ማህበረሰቡን በሁሉም የልማት መስኮች በባለቤትነት በማሣተፍ በዘንድሮው ክረምት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ርብርብ የሚደረግበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

በመድረኩም በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች የልማት ግቦችን ለማሳካት በተደረገ ርብርብ አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ይህንን ውጤት ማስቀጠል እና የማህበረሰቡን ባለቤትነት በሁሉም የልማት መስኮች ለማረጋገጥ የዘንድሮ ክረምት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ የሚደረግበት ወቅት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የክረምት ዘርፈ-ብዙ ሥራዎችን ለማሣካት በየደረጃው የክትትልና ድጋፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡

አመራሩን ፈፃሚን በማነሳሳት መልካም አፈጻጸሞች እና ምርጥ ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች እንዲሰፉ እድል በመፍጠር፣ በጉድለት የታዩ ጉዳዮች እና ማነቆዎችን በጋራ ተረባርቦ መፍታት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.