የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበለጠ እንዲጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በወጣቶች ዘንድ ባህል እየሆነ የመጣው በጎ ፈቃድ አገልግሎት የበለጠ እንዲጠናከር ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ ።
በጎነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታ እናረጋግጣለን በሚል መሪ ሃሳብ ከተማ አቀፍ ስፖርታዊ ፌስቲቫል በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል ።
በስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የስፖርት ቤተሰቡ ተሳትፈዋል ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ ÷ በወጣቶች ዘንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እየሆነ መምጣቱን እናበአገልግሎቱ በተለይም አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ወጣቶች ማህበረሰቡን ለማገልገል በመነሳታችሁ ትልቅ ክብርና ድጋፍ የምንሰጠው ነው” ሲሉም ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል።
በጎነት ገንዘብ የማይጠይቅ የህሊና ተነሳሽነትን ብቻ የሚፈልግ መሆኑን አስታውሰው ወጣቶች በጎነትን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል ።
ከተማ አስተዳደሩ በጎነት ከትውልድ ትውልድ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲሸጋጋር ድጋፍ እንደሚደርግም ገልጸዋል።