በእሳት አደጋው የተቃጠለው የገበያ ማዕከል ዳግም እስከሚገነባ በጊዜያዊነት የገበያ ማዕከል ይቋቋማል- ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በእሳት አደጋው የተቃጠለው የገበያ ማዕከል ዳግም እስከሚገነባ በጊዜያዊነት የገበያ ማዕከል እንደሚቋቋም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለፁ፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ በጅግጅጋ ከተማ የገበያ ማዕከል የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አስመልክቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በሚደረጉ ድጋፍና ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸው÷ በእሳት አደጋው ሀብት ንብረታቸው ለወደመባቸው መፅናናትን ተመኝተው እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ እያደረጉ ጉዳት ለደረሰባቸው የክልሉ የጸጥታና የእሳት አደጋ ተከላካይ አባላት ደግሞ ከጉዳቱ እንዲያገግሙ ተመኝተዋል፡፡
በተጨማሪም እሳቱን ለማጥፋት ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የሚመራና የወደመውን የሀብት መጠን፣ እያንዳንዱ ዜጋ የወደመበት የንብረት መጠን የሚያጣራ እና ግልጽ የሆነ ምርመራና ምዝገባ የሚያደረግ ግብረሃይል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
ኮሚቴው በአዲስአበባ፣ በጅግጅጋና በሌሎች የሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ያከናውናልም ብለዋል።
በእሳት አደጋው የተቃጠለው የገበያ ማዕከል ዳግም እስከሚገነባ ድረስ በቀጣይ ሳምንታት አቅም ያላቸውና ትንሽ የንግድ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችሉ ዜጎች በጊዜያዊነት የሚሰሩበት የገበያ ማዕከል ግብረሀይሉ እንደሚያቋቁም ተናግረዋል።
ኮሚቴው በእሳት ቃጠሎው የወደመውን ሀብት ካጣራ በኋላ መንግሥት ጉዳት ለደረሰባቸው ነጋዴዎች የሚያደርግው ድጋፍ ይፋ እንደሚደረግ ገልፀው መሰል አደጋ ዳግም እንዳይከሰትም ዘመናዊ የገበያ ማዕከል እንዲገነባ አብራርተዋል።