Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 9 ወራት 538 የበይነ መረብ ጥቃቶች ደርሰዋል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በ2012 በጀት ዓመት 9 ወራት ውስጥ 538 የሳይበር ጥቃቶች መድረሳቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለፀ።

ከነዚህም ውስጥ 88.1 % የሚሆኑ ጥቃቶችን መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን፥ 11.9% በሂደት ላይ ናቸው ብሏል።

እጀንሲው እንደገለፀው ከተፈጸሙት የሳይበር ጥቃቶች ውስጥ 263ቱ በአጥፊ ሶፍትዌሮች (ማልዌር) የተፈጸሙ ሲሆኑ፥ 106 ወዳልተፈቀደ ሲስተም ሰርጎ በመግባት፣ 105 የድረ-ገፅ ጥቃቶች፣ 54 የመሰረተ-ልማት ቅኝት፣ 9 የሳይበር መሠረተ ልማቶችን ሥራ ማቋረጥ እንዲሁም አንድ በሳይበር ማጭበርበር የደረሰ ጥቃት ነዉ፡፡

በሃገሪቱ ባለፉት 9 ወራት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሳይበር ጥቃት የተፈጸመው አጥፊ ሶፍትዌሮችን (ማልዌር) በመጠቀም የተፈጸሙ ሲሆኑ ይህም ከአጠቃላዩ 48.9 በመቶው ወይም 263 ጥቃቶች እንደሆኑ የኤጀንሲው የሳይበር ጥቃት አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ዲቪዥን /ኢትዮ-ሰርት/ገልጿል፡፡

ከእነዚህ የማልዌር ጥቃቶች ውስጥም አጋች ማልዌር (Ransomware) አማካኝነት የመረጃ መንታፊዎች የተለያዩ ፋይሎችን በመቆጣጠር እና ፍላጎታቸውን ለድርድር በማቅረብ ገንዘብ የሚጠይቁበት አንዱ ስልታቸው ነዉ ብሏል፡፡

በሌላው ዘርፍ የሚመደበው የማልዌር ጥቃት ውስጥ ክሪፒቶከረንሲ ማይነር (cryptocurrency miner) ሲሆን፥ ይህም ከጀርባ ሆኖ ባለቤቱ ሳያውቅ የሲስተሙን ሪሶርስ ለክሪፒቶከረንሲ ማይነር የሚጠቀሙበት ነው።

ከዚህ ባለፈ የመረጃ መዝባሪዎች ጥቃት ለማድረስ ቦትማልዌር (Bot malware) የሚባለዉን እና የሳይበር አጥቂዎች ተጠቃሚው የሚሰራበትን አንድ ኮምፒውተር በመቆጣጠር በበይነመረብ የተሳሰሩት ሌሎች ኮምፒውተሮችን ለማጥቃት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነዉ፡፡

ዲቪዥኑ ባለፉት 9 ወራት ውስጥ የተከሰቱ ጥቃቶቹን ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን ከእነዚህ መካከል በተለያዩ ተቋማት ላይ የሳይበር ደህንነት ክፍተት ትንተና በማከናወን ለተቋማቱ ክፍተታቸውን በማሳወቅ የሳይበር ጥቃት ሳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል እና የሳይበር ጥቃት ከመከሰቱ በፊት ገና ቅኝት ላይ እያለ የመግታት ስራ ተከናውኗል።

የተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርሱ መግታት መቻል፤ በተፈጠሩት የሳይበር ጥቃቶች መሰረት አገልግሎት ተቋርጠው የነበሩ ሲስተሞች በፊት ይሰሩበት ወደ ነበረው ይዞታቸው ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ፤ በራንሰም ዌርጥቃት ተጠልፈው የነበሩ ሲስተሞች በማስፈታት አገልገሎት እንዲሰጡ የማድረግ፤ እንዲሁም ድጋሚ እንዳይጠቁ ደካማ ጎናቸው እንዲደፈን በማድረግ የመከላከል ስራ መስራቱን ገልጿል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣዉ እና በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ ሊከሰቱ ከሚችሉ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አሳስቧል፡፡

ኤጀንሲው የሃገሪቱን የኢንፎርሜሽን እና የኢንፎርሜሽን መሰረተ- ልማቶችን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም በመገንባት ብሄራዊ ጥቅሞችን በማስጠበቅ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.