ኢትዮጵያ እና ባሕሬን በቱሪዝም ዘርፍ በጋራ ለመሥራት መከሩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ባሕሬን በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር ለመሥራት በሚቻልበት ሁኔታ መከሩ፡፡
በባህሬን የኢትዮጵያ ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ ከባሕሬን የቱሪዝም ሚኒስትር ፋጢማ አልሳይራፊ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በተመድ የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት ዕውቅና ያላቸው በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የመስኅብ ስፍራዎች ያሏት ሀገር መሆኗን ቆንስል ጄኔራሉ አንስተውላቸዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት በርካታ አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የመስኅብ ስፍራ ፓርኮች መገንባታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰፊ የጎብኚ መዳረሻዎች እንደሚገኙም አውስተዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት በቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች የዘርፉን ባለሙያዎች በማገናኘት ወደ ሥራ ማስገባት እንዲቻል መሥራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው አምባሳደሩ ሐሳብ ያቀረቡት።
ሚኒስትሯ በበኩላቸው የጎብኚ ፍሰቱን ለማጠናከር የሁለቱ ሀገራት ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲመቻች በትብብር እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡