Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ቻይና የሕግ ማስከበር ትብብር ማዕከልን በኢትዮጵያ ለማቋቋም ስምምነት ላይ ተደረሰ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በቻይና የሕዝብ ደኅንነት ምክትል ሚኒስትር ቼን ስዩአን ከተማራ ልዑክ ጋርተወያይተዋል፡፡

ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷በቅርቡ ቻይናን በጎበኙበት ወቅት የሀገራቱን የፖሊስ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር፣ የሁለትዮሽ የከፍተኛ ኃላፊዎችና የባለሙያ ቡድን የጋራ መድረክ ለመፍጠር እና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል መወያየታቸውን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ የኢትዮ-ቻይና የህግ ማስከበር ትብብር ማዕከልን በኢትዮጵያ ለማቋቋም እና የሕግ አስከባሪ አከላትን አቅም ለማጠናከር በውይይቱ ላይ ማንሳታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የቆየ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት ጠቁመው÷ ለሀገራቱ አጋርነት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በፀጥታ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና ፖሊስ ለፖሊስ ትብብርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ቼን ስዩአን በበኩላቸው ÷ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግረዋል፡፡

የኢትየጵያ ፌደራል ፖሊስ እያስገነባ ያለውን የፎረንሲክ የልዕቀት ማዕከል በማቴሪያል፣ በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሀገራቱ የፖሊስ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ባደረጉት የመጀመሪያ ስብሰባ የፖሊስ አመራሮች፣ የኦፊሰሮችን፣ የከፍተኛ ባለሙያዎችን ልምድ ልውውጥ በማድረግ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በቀጣይም በፈረንጆቹ በ2025 የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ በቻይና የሁለትዮሽ የጋራ መድረክ ለማካሄድ ተስማምተዋል፡፡

ለአፍሪካ ጭምር የሚያገለግለውን የኢትዮ-ቻይና የህግ ማስከበር ትብብር ማዕከልን በኢትዮጵያ ለማቋቋም፣ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል፣ ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ ላይ በጋራ ለመስራት እና የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለመለዋመጥ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት የሚገኙ የዜጎች ደኅንነትን ለመጠበቅ እና በኢትየጵያ የሚገኙ የቻይና ፕሮጀክቶችን እና የተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ ተስማምተዋል፡፡

በሌላ በኩል መረጃን በመለዋወጥ የሁለቱን ሀገራት ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ቻይና ለኢትዮጵያ ፖሊስ የትምህርት ዕድል በመስጠት አቅም ለማጠናከር የጋራ መግባባት ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.