በተለምዶ “ቆሼ ” ተብሎ በሚጠራው የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ የችግኝ ተከላ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በተለምዶ “ቆሼ ” ተብሎ በሚጠራው የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ፥ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ማሾ ኦላና ተገኝተው አሻራቸውን አሳርፈዋል።
አቶ ጥራቱ በየነ በዚሁ ወቅት አዲስ አበባም ሆነ ኢትዮጵያ ያደገች፣ የበለፀገች፣ ለመጪው ትውልድ የተመቸች እንድትሆን ነገን ዛሬ ዝቅ ብለን ፣ አፈር ነክተን እየተከልን በትጋት መስራታችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።
አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፊታችን ሐምሌ 10 ቀን በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞች የመትከል ጥሪ በስኬት እንዲፈፀም ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ማሾ ኦላና በበኩላቸው ፥ ፅዱ፣ አረንጓዴና ውብ የሆነች ከተማ ለመፍጠር የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ላለው ጥረት ዜጎች የየድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በረጲ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ችግኞችን መትከል ከስፍራው የሚወጣውን መርዛማ ፍሳሽና ጋዝ ለመከላከል የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በዚህ ቦታ የሚካሄድ የችግኝ ተከላ በከተማው ላለፉት 50 ዓመታት በላይ በቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራነት እያገለገለ ላለው የረጲ ቆሼ ስፍራና ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ጥበቃ ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡
በመርሐ ግብሩ 30 ሺህ ችግኝ እንደሚተከል ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።