Fana: At a Speed of Life!

የሳንሱሲ- ታጠቅ -ኬላ መንገድ ስራ በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳንሱሲ- ታጠቅ -ኬላ መንገድ ስራ በአፋጣኝ ችግሮቹ ተቀርፈው ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የመስክ ቅኝት ዛሬ ተካሂዶል ፡፡
 
በጉብኝም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሰልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ፤ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ፣ የአካባቢው የመስተዳድር አካላትን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
 
የስራ ኃላፊዎቹ የሳንሱሲ- ታጠቅ – ኬላ 13 ነጥብ 56 ኪ.ሜ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ስራ ያለበትን አጠቃላይ ደረጃ እና ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች በቦታው በመገኘት ተመልክተዋል ፡፡
 
ዋና ዳይሬክተሩ ኢ/ር ሀብታሙ ተገኘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመንገዱ ግንባታ ላይ ያለው እንቅስቃሴ መነቃቃት እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል ።
 
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የወሰን ማስከበር ውስብስብና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያለ በመሆኑ አፈጻጻሙ የሚጠበቀውን ያህል እንዳይሆን ምክንያት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
 
የክረምት ወቅት እየተቃረበ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዳይጉላላ ተቋራጩ ተጨማሪ የስራ ሰዓት ተጠቅሞ ግንባታውን አንዲያፋጥን አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
 
የመንገዱ ስራ ተጠናቆ ተገቢውን ግልጋሎት መስጠት እንዲችል በመንገዱ ወሰን ክልል ውስጥ ያሉ የመኖርያ ቤቶች እና የዩቲሊቲ ተቋማት (ኤሌክትሪክ ፖል ፣ የቴሌ ኦፕቲክ ፋይበር እና የውሃ መስመር ) በወቅቱ እና ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
 
አሁንም የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን ለማፍጠን መሰናክል የሆኑ የወሰን ማስከበር ስራዎች ያልተጠናቀቁ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
 
በህዳር ወር 2010 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው መንገዱ በእስካሁኑ ስራ የአፈር ሙሌትና ድልዳሎ፣የውሃ መፋሰሻ ቱቦ ቀበራ እና 16 ሜትር ርዝመት ያለው የገፈርሳ ወንዝ ድልድይ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሰልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
ከዚህም ባለፈ በወሰን መስከበር ነጻ በሆኑ የመንገዱ ግራ እና ቀኝ በአንዱ አቅጣጫ የአስፋልት ማንጠፍ ስራው መከናወኑን ይገኛል ተብሏል።
 
የሳንሱሲ – ታጠቅ – ኬላ ፕሮጀክት ከ820 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገባ ያለ መንገድ ነው፡፡
 
ከሁለት አመት በፊት የተጀመረው ፕሮጀክቱ ተግዳሮቶቹ ተቀርፈው ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል ፡፡
 
መንገዱ ሲጠናቀቅ ከዚህ ቀደም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ይከሰት የነበረውን መጉላላት ያስቀራል ተብሎ ታምኖበታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.