በክልሉ በአንድ ጀምበር 10 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንድ ጀምበር 10 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳዳር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል፡፡
ዕለቱ ታሪክ የሚሰራበት ቀን በመሆኑ፣ የክልሉ ሕዝብ ከማለዳ ጀምሮ በዚህ ሀገራዊ ጥሪ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ በርዕሰ-መስተዳድሩ ጥሪ መቅረቡን የክልሉ ኮሙኒኬሽን በመረጃው አመላክቷል፡፡
በክልሉ ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ሰኔ 24 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ መጀመሩን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተያዘው ክረምት በአጠቃላይ 55 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ዕፅዋት እና የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።