Fana: At a Speed of Life!

ኔቶ የዩክሬንን የአባል ሀገርነት ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ ማድረጉ ዜሌንስኪን አስቆጣ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የዩክሬንን የአባል ሀገርነት ጥያቄ ለጊዜው አለመቀበሉ ተገለጸ፡፡

የኔቶ አመራሮች የዩክሬን በወታደራዊ ጥምረቱ ውስጥ የመቀላቀል ጥያቄ ለወደፊቱ ይታያል ብለዋል፡፡

ሁኔታው የሀገሪቷን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪን ማስቆጣቱን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የ31ዱ የኔቶ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሀገራት ከትናንት ጀምሮ የሁለት ቀናት ጉባዔ በሊቱኒያ መዲና ቪልኒየስ ማካሄድ ጀምረዋል፡፡

የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱ መሪዎቹ በትናንት መግለጫቸው የወደፊት የዩክሬን አባል ሀገራቱን የመቀላቀል ጉዳይ ዕርግጥ ነው ብለዋል መቼ እንደሆነ ግን ጊዜ ቆርጠው አልተናገሩም፡፡

ዩክሬን የጦር ቃል ኪዳን ድርጅቱን እንድትቀላቀል ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸውና አባል ሀገራቱ መሥማማት እንዳለባቸውም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

በመሆኑም ዩክሬን ኔቶ የሚጠይቀውን የአባልነት የድርጊት መርሐ-ግብር ብታቀርብም ጊዜው ገና ነው በሚል በጉባዔው ውድቅ መሆኑ ነው የተሰማው፡፡

በቪልኒየሱ ጉባዔ ላይ ለታደሙት እና ከሩሲያ ጋር በጦርነት ውስጥ ለሚገኙት ፕሬዚዳንት ቮሎድሜር ዜሌንሲኪ እውነታውን ለመቀበል እንደከበዳቸው ተገልጿል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው “ለወደፊት የአባልነት ግብዣውም ሆነ ለዩክሬን የአባልነት ጥያቄ ምላሽ የጊዜ ገደብ ካልተበጀለት (ጉባዔው) ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እና የማይረባ ነው” ሲሉ አስፍረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.