Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከኮሪያ ጋር በመተባበር የ“ስማርት ሲቲ” ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ዕውን ልታደርግ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ“ስማርት ሲቲ” ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ለማስጀመር የሚያስችል የቅድመ-ዝግጅት ሥምምነት ላይ ተደረሰ፡፡

የሦስትዮሽ የቅድመ-ዝግጅት የሥምምነት ፊርማቸውን ያኖሩት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ፣ የኮሪያ መንግስት የፕሮጀክት ኮንሰርቲየም እና የኢኮ-አረንጓዴ ስማርት ሲቲ ከተሞች የግንባታ ፕሮጀክትን የሚያስተባብረው የሀገር ውስጥ አጋርና አማካሪ ሀገሬ ኃ.የተ.የግል ድርጅት ጋር መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሥምምነቱ ሁሉን አቀፍ ኢኮኖሚያዊ አጋርነትንና የትብብር ዘርፎችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ያጠቃልላልም ነው የተባለው፡፡

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን ÷ ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የሚተገበሩት ፕሮጀክቶች ÷ የከተማ ግብርናን ፣ የቡና እርሻን ፣ የጤና አጠባበቅን ፣ የሙያ ትምህርትን ፣ የኤሌክትሮኒክ ሥርዓትን እና የብሔራዊ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስን ያማከሉ መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የፕሮጀክቶች ዕውን መሆን የመንግስታቱን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከርና በንግድ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማጎልበት ያስችላልም ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም የሚዘረጋው ሥርዓት ሀገራቱን በሂደት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመግባት እንደሚያስችላቸው በሥምምነት ሠነዱ ላይ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.