የኦሮሚያ ክልል የ2015 አፈፃፀም ተገመገመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ የ2015 ዓ/ም አፈጻፀምና የ2016 ዓ/ም እቅድ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ በ2015 በጀት ዓመት በፈተና ውስጥ አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመሆን በከፍተኛ መስዋዕትነት መልካም ውጤቶች አስመዝግቧል ብለዋል።
አመራሩ በአንድ በኩል ሰላምን እያፀና በሌላ በኩል ደግሞ የታቀዱ የልማት ስራዎችን ማጠናቀቅ ዓላማ አድርጎ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅበትም ነው ያስታወቁት።
በየትኛውም ችግር ውስጥ የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ የሚቀጥል እና የሚሳካ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፥ በስራ ላይ ያጋጠሙ ጥንካሬዎችና ድክመቶች በመለየት ጥንካሬዎች እንዲቀጥሉና የተለዩ ድክመቶች ደግሞ እንዲስተካከሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት የተጀመረው የውይይት መድረክ የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀምን ከገመገመ በኋላ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ተወያይቶ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በመራኦል ከድር