ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መስኮች በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ ናት – ሴናተር ኢጎር ሞሮዞቭ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መስኮች በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴ ሰብሳቢ ሴናተር ኢጎር ሞሮዞቭ ገለጹ፡፡
ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ጉባዔ ቅድመ ውይይት የሩሲያ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ፣ የንግድ ማኅበረሰብ ተወካዮች እና የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ሴናተር ኢጎር ሞሮዞቭ ሩሲያ በትምህርት ፣ በንግድና እና በኢንቨስትመንት መስኮችም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራት እንደምትፈልግም በቅድመ-ውይይቱ መድረክ ላይ አንስተዋል፡፡
ሩሲያ በጠፈር ምርምር መስክ ያላትን የዳበረ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴ በአፍሪካ ካሉት አራት መሥሪያ ቤቶች አንዱን በአዲስ አበባ መክፈቱ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኛ መሆኗን የሚያሳይ ነውም ብለዋል።
የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተሽከርካሪዎች ፣ በትራክተር እና በሌሎች የእርሻ መሳሪያዎች ምርትና መገጣጠም ሥራ ላይ በመሰማራት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ሴናተር ኢጎር ገልጸዋል።
ሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ የኢኮኖሚ ጉባኤ ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ብሎም ከመላው አፍሪካ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የባህል እና ሰብአዊ ድጋፍ ትብብር ለማጠናከር የሚያግዝ መድረክ እንደሚሆን ዕምነታቸው መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያና ሩሲያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች ለመተባባር የሚያስችል ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
ሩሲያ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ የምታደርገው ትብብር የኢትዮጵያን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በእጁጉ እንደሚያግዛት ጨምረው ገልጸዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ