ኢትዮጵያ እና ካሜሩን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከካሜሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌጄዩን ምቤላ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ነገ መካሄድ ከሚጀመረው 43ኛው የአፍሪካ ኀብረት የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በፊት የተደረገ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
በውይይታቸው በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና በባለ ብዙወገን ጉዳዮች የሀገራቱን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ ትኩረት አድርገው መክረዋል።
ከዚህ ባለፈም የሀገራቱን የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እና ፖለቲካዊ ምክክራቸውን ለመቀጠል መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
አቶ ደመቀ ለሚኒስትሩ በፕሪቶሪያ ስለተደረሰው የሰላም ሥምምነት አተገባበር ገለጻ ያደረጉላቸው ሲሆን፥ ካሜሩን በዓለም አቀፉ መድረክ ለኢትዮጵያ ላሳየችው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።