Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ  አመራሮች በሰላምና ደኅንነት ላይ መከሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በሰላምና ደኅንነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያዩ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ÷ አዲስ አበባ ከተማ የብዙ ሁነቶች ማዕከል፣ የአፍሪካ መዲና እና የበርካታ ዲፕሎማቶች መኖሪያ መሆኗን አብራተዋል፡፡

ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እንዲጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች መጠናከርና መደራጀት የህዝብና የመንግስት  ንብረት ከመጠበቅ ባለፈ የከተማዋ ሰላም የተረጋጋ እንዲሆን አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ የጥበቃ ኤጀንሲዎች ከምልመላ፣ ከስልጠና፣ ከሥምሪት እና ከክትትል መጓደል የተነሳ የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ÷ በአዲስ አበባ ከተማ የግል ጥበቃ ተቋማት ቅጥር በሚያካሂዱበት ወቅት የተቀጣሪዎችን ማንነት በሚገባ ሳያረጋግጡ በሐሰተኛ ሰነድ በመቅጠራቸው የፀጥታ ችግሮች መፈጠራቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ባንኮች፣ የግል ተቋማት፣ የንግድ ማዕከላት እና የግለሰብ ንብረቶች በቀጠሯቸው የጥበቃ ሠረተኞች እየተዘረፉ መሆናቸውን ነው ያብራሩት፡፡

በውይይት መድረኩ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋሉ ወንጀሎችን የሚዳስስና የወንጀል አዝማሚያዎችን ያመላከተ ጥናታዊ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.