አቶ ደመቀ መኮንን ከጋምቢያ እና ማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጋምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማመዱ ታንጋራ (ዶ/ር) እና ከማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ቴምቦ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ በኬንያ እየተካሄደ ከሚገኘው 43ተኛው የአፍሪካ ኀብረት የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ጎን ለጎን ነው የተደረገው፡፡
አቶ ደመቀ÷ከጋምቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማመዱ ታንጋራ (ዶ/ር) ጋር ባደረጉት ውይይት በሀገራቱ መካከል ባለው የሁለትዮሽ እና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ በሀገራቱ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
አቶ ደመቀ ከማላዊ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ቴምቦ ጋርም በሀገራቱ የሁለተዮሽ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡