Fana: At a Speed of Life!

ለፅንፈኛ ኃይሎች ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽብር ወንጀል ለመፈፀም ለሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ ኃይሎች የሎጅስቲክ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ በመገናኛ አካባቢ በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ ያለው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ የጥርጣሬ መነሻ ምክንያቶችን ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄና የተጠርጣሪዎችን መከራከሪያ ነጥብ መርምሮ ተገቢ ነው ያለውን ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ዳንኤል አስረስና ወንዶሰን ጣለባቸው ይባላሉ።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በኢ- መደበኛ አደረጃጀት ተደራጅተው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ አካባቢ ሽብር ለመፍጠር ከሚንቀሳቀስ ፅንፈኛ ኃይል ጋር ግንኙነት በማድረግ የሎጅስቲክ አቅርቦት በማቅረብ መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎት አብራርቷል።

በዚህም መነሻ በአመራሮች ላይ ግድያን ለማስቀጠል በኢ- መደበኛ አደረጃጀት በመደራጀት ከሚንሳቀስ አንድ አመራር ግለሰብ ጋር በመገናኘት ደህንነቱ የተጠበቀና የማይጠለፍ ሞባይል ግዢ እንዲፈጸምለት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ተጠርጣሪዎቹ ደህንነቱ የተጠበቀ የሞባይል ስልክ ልከውለታል በማለት ፖሊስ የጥርጣሬ መነሻ ምክንያቱን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ይህን ደህንነቱ የተጠበቀ ሞባይል ስልክ ለፅንፈኛ ኃይል አመራር መላካቸውን አምነው ይቅርታ ጠይቀው ቃላቸውን ሰጠዋል በማለትም ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው÷ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነትእንደሌላቸው እና ቃላቸውን የሰጡት በጫና መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል።

መርማሪ ፖሊስ ግለሰቦቹ ምንም ጫና ሳይደረግባቸው በገዛ ፍቃዳቸው ወንጀሉን መፈጸማቸውን ገልጸው ፤ቃላቸውን ማስመዝገባቸውን ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በዋልንበት ወቅት ሰብዓዊ መብታችን ተጥሷል በማለት አቤቱታ አቅርበዋል።

አቤቱታውን ተከትሎ ፖሊስ በመገናኛ አካባቢ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት በፖሊስ በኩል ምንም ጥሰት እንዳልተፈጸመባቸው ገልጾ መልስ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪ ዳንዔል÷ የስራ ድርሻው ምን እንደሆነ በችሎቱ ዳኛ በተጠየቀበት ወቅት መምህርና የዲሽ ሰራተኛ ነኝ በማለት አስመዝግቧል።

ሁለተኛው ተጠርጣሪን በሚመለከት በተሽከርካሪ ሹፌርነት ሙያ እንደሚተዳደር ገልጾ ÷ ከሁለት ወር በፊት መከላከያ ሰራዊትን በተሽከርካሪ በማጓጓዝ ”ለግዳጅ የበኩሌን አስተዋጾ አበርክቻለሁ ” በማለት ለችሎቱ አስረድቷል።

በዚህም መሰረት ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድ የጠየቁ ሲሆን ፥ መርማሪ ፖሊስ የዋስትና ጥያቄያቸውን በመቃወም የመከራከሪያ ነጥብ አንስቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ የማጣሪያ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊነትን በማመን የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ ተጨማሪ የማጣሪያ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.