Fana: At a Speed of Life!

የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የእዳ ስረዛ መከራከሪያ በሎውረንስ ፍሪማን እይታ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ዝቅተኛ ገቢ ያቸው አዳጊ ሀገራትን ከኮቪድ-19 ተፅእኖ ለመጠበቅ እዳቸውን መሰረዝ አስፈላጊ መንገድ መሆኑን ያቀረቡት ሀሳብ ብሄራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲዎች ሊገዙበት የሚገባ መርህ መሆኑን አውቁ የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኙ እና ፀሃፊው ሎውረንስ ፍሪማን ገለፁ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኒው ዮርክ ታይምስ መፅሄት ላይ ባወጡት ፅሁፍ አበዳሪ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አዳጊ ሀገራትን ከኮቪድ-19 የከፋ ተፅዕኖ ለመታደግ የብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘም ሳይሆን ብድርን መሰረዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ሎውረንስ ፍሪማን ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት ትክክል መሆኑን ያነሳሉ፥ ኢትዮጵያን የመሰሉ አዳጊ ሀገራት ከገቢያቸው ውስጥ ግማሽ የሚሆነውን ለብድር ክፍያ እንደሚያውሉ በማንሳት።

እነዚህ ሀገራት ከኮሮና ቫይረስ በተጨማሪ በበረሃ አንበጣ፣ በምግብ እጥረት እና በዝቅተኛ የጤና ዘርፍ በጀት እየተሰቃዩ ባለበት ሁኔታ ብድርን መጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ወንጀል ባይሆን እንኳን ከሞራል አንፃር ተቀባይነት የሌለው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የጠየቁት አስቸኳይ የዕዳ ስረዛ በተለይም በአፍሪካ ከኮቪደ-19 ጋር ተያይዞ እየከፋ ለመጣው የምግብ ዋስትና ችግር አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው።

እንደፀሃፊው በአፍሪካ ኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተወሰዱ እንደ ድንበር መዝጋት፣ ሰዎች በቤት እንዲቆዩ መደረጉ ይህንንም ተከትሎ ዜጎች የገቢ መጠን መቀነሱ እና የሸቀጦች እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ቀደሞም በአህጉሪቱ የነበረውን የምግብ ዋስትና ችግር ከፍ አድርጎታል።

የዓለም ምግብ ድርጅት ሪፖርትን ዋቢ በማድረግም በፈረንጆቹ 2020 በኮቪድ -19 ምክንያት የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ከ135 ሚሊየን ወደ 265 ሚሊየን እንደሚያድግ ያነሳሉ።

የኸው ሪፖርት በፈረንጆቹ 2019 የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ከነበራቸው ሀገራት መካከል አምስቱ በአፍሪካ እንደነበሩ በማንሳትም ናይጀሪያን፣ ኢትዮጵያን፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንን እናዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎን ዘርዝሯል።

ሎውረንስ ፍሪማን በመሆኑም የብድር ስረዛ አስፈላጊ ቢሆንም በተጨማሪነት የአፍሪካ ሀገራት ችግር የሆነባቸውን የጤና መሰረተ ልማታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያስችል አዲስ የብድር አቅርቦት ሊኖርም ይገባል ሲሉ ነው የሚያስረዱት።

የአፍሪካ ሀገራት የጤና፣ የመንገድ፣ የሀይልና ባቡር መስረተ ልማታቸውን እንዲያሻሺሉ በትሪሊየን ዶላር የሚቆጠር ብድር ሊቀርብላቸው ይገባል ባይ ናቸው።

በአጠቃላይ ለአፍሪካ የሚዘጋጀው የፋይናንስ ስርዓት ብድርን መሰረዝን፣ ለመሰረት ልማት ግንባታ የሚውል አዲስ የብድር አቅርቦት መፍጠርን፣ በመሰረተ ልማት ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ማስቻልን፣ ዘመናዊ የጤና መሰረተ ልማትን ማቋቋምን እና ማምረቻ እና ግብርና ዘርፍን ማሳደግን ያካተተ መሆን አለበት ብለዋል።

ብድሮች ማህረሰብን መጠቅም ሲሳናቸው የአከፋፈል ሁኔታቸው ዳግም ሊታይ ወይም ሊሰረዙ ይገባል የሚሉት ፀሀፊው ይህም ከዚህ በፊት ተሞክሮ ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.