ቢዝነስ

የሲዳማ ክልል ገቢዎች ቢሮ 8 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

By Melaku Gedif

July 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የሲዳማ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይሉ ጉዱራ÷በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ግብር ከፋዮች እና መዘጋጃ ቤት አገልግሎት 10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል

እቅዱን በተሻለ ሁኔታ ለማሳካትም አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት እንዲሁም ፖሊሲዎችን በማሻሻል ግብር ከፋዮች በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍሉ የማድረግ ስራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ግብር ከፋዮች እና መዘጋጃ ቤት አገልግሎት 8 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን አቶ ሃይሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ገቢው በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ 37 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች እንደተሰበሰበ ጠቁመው÷ አፈጻጸሙም ከባለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡

በቀጣዩ 2016 በጀት ዓመትም 13 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን አቶ ሃይሉ ጠቁመዋል፡፡

የገቢ ስወራን መቆጣጠር፣ የተሻለ ዘመናዊ አሰራር መዘርጋት፣ ሀሰተኛ ደረሰኝን መከላከል እና መረጃ አያያዝን ማዘመን በቀጣይ በትኩረት የሚከናወኑ ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

 

በመላኩ ገድፍ