የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ 560 ሺህ የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ 560 ሺህ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ 1ሺህ 835 ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ መዋዕለ -ንዋይ ፈሰስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የቻይና ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እና ሀገሪቷ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የበለጠ ዕድገት ለማስመዝገብ የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፉ እንደሚሠሩም ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተፈጠረው አስቻይ የኢንቨስትመንት ምኅዳር በርካታ የቻይና ኩባንያዎች እንደተነቃቁና በኢትጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ እንደሚመጡም ያላቸውን ዕምነት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
የልማት ሥራ ÷ ሥርዓት ያለው የሥራ ቅጥር እና ሥምሪት፣ የተሻሻለ የኑሮ ሁኔታ ፣ የባሕል ዕድገት እና ጤናማ የሥራ ሥነ-ምኅዳር ይፈልጋልም ብለዋል፡፡
ለዚህ ዕውን መሆንም በኢትዮጵያ የሚመለከተው አካል ማሕበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ቻይና በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ምንጊዜም ዝግጁ መሆኗን ገልጸው ላለፉት አሥርት ዓመታት በ”ቤልት ኤንድ ሮድ” መርሐ-ግብር የተሠሩ ሥራዎችም በኢትዮጵያ እና በቻይና የትብብር ሥራዎች የሚታይ ዕድገት እና መሻሻል ማሳየታቸውን አብራርተዋል፡፡
በመርሐ-ግብሩ የቻይና ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ፣ የባቡር የትራንስፖርት አገልግሎት ግንባታዎች ፣ የመንገድ እና የኮሙኒኬሽን መሠረተ-ልማቶችን መሥራታቸውንና ኢትዮጵያ የተለመችውን ዘላቂ የልማት ዕቅድ ዕውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን ያላትን ፍላጎት ቻይና ትደግፋለችም ነው ያሉት አምባሳደሩ።
በወንደሰን አረጋኸኝ