ደቡብና ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተሰማ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ደቡብ ኮሪያ እና ሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ሀገራቱ የጦር ማሳሪያ ተኩስ ልውውጡን ያደረጉት በሁለቱ ሀገራት ድንበር መካከል በሚገኘው ከጦር መሳሪያ ነፃ በሆነው ቀጠና ላይ መሆኑም ተነግሯል።
የሴኡል ጦር እንዳስታወቀው ከሰሜን ኮሪያ የተተኮሰ ጥይት የድንበር ከተማ በሆነችው ቼርዎች ውስጥ አንድ የደቡብ ኮሪያ ድንበር ጠባቂን መትቷል።
ይህንን ተከትሎም የደቡብ ኮሪያ ጦር የጦር መሳሪያ ተኩስ ምላሽ እና ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ያስታወቀ ሲሆን፥ ከሰሜን ኮሪያ በኩል ግን ጉዳት ስለመድረሱ የተገለፀ ነገር የለም ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ የተኮሰችው ለ21 ቀናት ከእይታ ተሰውረው የነበሩት የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ብቅ ካሉ ከ24 ሰዓታት በኋላ መሆኑ ታውቋል።
በቅርብ ወራትም በሰሜን ኮሪያ ውስጥ የወታደሩን ዝግጁነት የሚያጠናክሩ ከትክክለኛ ጦርነት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ወታደራዊ ልምምዶች ሲደረጉ መቆየታቸውም ነው የተገለፀው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል እንደዚህ አይነት የጦር መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 የተካሄደ ሲሆን፥ የዛሬውም ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ፕሬዚዳንት ሙን ጄይ ኢን እና ኪም ጆንግ ኡን ከተገናኙ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምን ለማስፈን በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው አይዘነጋም።
ሁለቱም ወገኖች የተለያዩ ወታደራዊ ስመምነቶችን መፈራረማቸውን የሚታወስ ሲሆን፥ ሆን ተብለው የሚደረግ የጦር መሳሪያ ተኩስ ግን ስምምነቱን ሊያፈርስ ይችላል ተብሏል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ