Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግብጽ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ ነበር – ዶክተር ለገሰ ቱሉ

 

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግብጽ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብጽ ካይሮ በተካሄደው ‘የሱዳን ጎረቤት ሀገራት ጉባዔ’ የነበራቸውን ተሳትፎ አስመልክቶ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግብጽ ቆይታቸው ሦስት አበይት ተግባራትን በተሳካ መልኩ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በመጀመሪያ መሰረተ-ልማት የተሟሉለት ዘመናዊውን አዲሱ ካይሮን መጎብኘታቸውን ጠቁመው፥ በዚህም የኃይማኖት ተቋማት፣ ሙዚየምና ሌሎች ሥፍራዎችን መጎብኘታቸውን አስረድተዋል።

ጉብኝታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ የሚሆን ልምድ መቀመራቸውን ተናግረዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የተሳካ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት ሀገራቱ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ከሥምምነት መድረሳቸውንም ነው የተናገሩት።

ሀገራቱ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ቀጣይ የትብብር ዘርፎች እንዲሁም በአካባቢያዊ ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው መምከራቸውን አስረድተዋል።

የጋራ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት ያደረገ ትብብር ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅምና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን መሪዎቹ ከመግባባት ደርሰዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ሁለቱ ሀገራት በመተማመን መንፈስ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን አለመረጋጋት ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም በማንሳትም፥ ይህም ለቀጣናው ልማት ወሳኝ መሆኑን መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል ነው ያሉት።

ይህንን ለማድረግ ሁለቱ ሀገራት ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በመከባበርና በሰጥቶ መቀበል መርህ አጋርነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው መወያየታቸውን አውስተዋል።

የሱዳንን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት በግብጽ ካይሮ የመከሩት የጎረቤት ሀገራት መሪዎች ተፋላሚ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ሥምምነት እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በችግር ላይ የሚገኙ ሱዳናውያን ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙና ሁለቱ ኃይሎች ሁሉን አቀፍ ውይይት በፍጥነት እንዲጀምሩ መሪዎቹ ከሥምምነት መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።

ይህም ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የሱዳን ሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ መልኩ መከናወን እንዳለበት መሪዎቹ የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፋቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በተመሳሳይ የሱዳን ችግር እንዲፈታ እንዲሁም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን ጽኑ አቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውንም አብራርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.