በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለአገልግሎት ክፍት ሊሆኑ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ7 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ በአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተገነቡ 12 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ከነገ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ለንባብ ያበቁት የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ገቢ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚሰሩ የልማት ስራዎች እንዲውል ማድረጋቸው ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከመጽሐፉ ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለስፖርት ማዘውተሪያና ለሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ እንዲውል ግብ አስቀምጦ ሲሰራ ቆይቷል።
የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀን እንደገለጹት÷ ከመጽሐፉ ሽያጭ በተገኘ ገቢ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትና የሕጻናት መጫዎቻዎች ተገንብተዋል።
ግንባታውንም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሶስት ወር በፊት ማስጀመራቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዚሁ መሰረት በመጀመሪያው ዙር በየካ እና ቦሌ ክፍለ ከተሞች የተሰሩ 12 ፕሮጀክቶች ከነገ ጀምሮ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ከሚመረቁት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል የፉት ሳል፣ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎችና የሕጻናት መጫወቻ ስፍራዎች ይገኙበታል።
በተጨማሪም የእግር ኳስ ውድድር የሚደረግባቸው መካከለኛ ስታዲየሞች መካተታቸውን ጠቅሰው በተለይም ለወጣቶችና ለክለቦች የመለማመጃ ስፍራ እጥረትን ያቃልላሉ ብለዋል የቢሮው ኃላፊ።
የግንባታው ወጪ የተሸፈነው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመጀመሪያው ዙር ከመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ ከተሰበሰበው ከ150 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመጽሐፉ ሽያጭ አሁንም የቀጠለ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያት በሁለተኛ ዙር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን እያጠናቀቁ ለአገልግሎት ክፍት የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡