የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ላይ ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐምሌ 10 ቀን ለሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጥሪ አቀረቡ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ÷ የደቡብ ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች ናቸው ጥሪውን ያቀረቡት።
በደቡብ ክልል በአንድ ጀምበር 110 ሚሊየን ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን ÷ ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ አሻድሊ ሃሰን ÷ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንድ ጀምበር የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው 10 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ÷ በክልሉ 25 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የክልሉ ነዋሪዎችም በዕለቱ ታሪክ እንዲሰሩ ጋብዘዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም 20 ሚሊየን ችግኝ እንደሚተከል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የገለጹ ሲሆን በመርሐ-ግብሩ ከ1 ሚሊየን በላይ ሕዝብ እንደሚሳተፍ ተናግረዋል፡፡
ርዕሳነ-መስተዳድሮቹ በዕለቱ በተዘጋጀው የችግኝ መትከያ ቦታ በመገኘት አረንጓዴ ዐሻራችንን እናሳርፋለንም ነው ያሉት፡፡
ኅብረተሰቡም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ወደ ተዘጋጀለት የችግኝ መትከያ ቦታ በመሄድ አረንጓዴ ዐሻራውን እንዲያሳርፍ እና የታሪኩ ተካፋይ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ