Fana: At a Speed of Life!

በሳሪስ አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ለጊዜው መቋረጡ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ በሚገኘው የባቡር መስመር መሰረተ ልማት ላይ አደጋ በማጋጠሙ የቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎቱ መቋረጡ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር  አገልግሎት የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሔኖክ ቦጋለ እንደገለጹት፥ ዛሬ እኩለ ቀን የባቡር መስመሩ ላይ አደጋ ደርሷል።

አደጋው ሳሪስ ልዩ ስሙ ሬይስ ኢንጂነሪንግ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ኮንቴይነር የጫነ ከባድ ተሽከርካሪ በባቡር ሐዲድ መሰረተ ልማቱ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

በዚሁ ሳቢያም ከሳሪስ አቦ ወደ ስቴዲየም ከስቴዲየም ወደ ሳሪስ አቦ የሚደረገው የባቡር ምልልስ በጊዜያዊነት መቋረጡን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታትና መስመሩን ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ነው ያመለከቱት።

በመሰረተ ልማቱ ላይ ከደረሰው አደጋ ውጪ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም መገለፁን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.