የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ጥንካሬውን እንዲያስቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዘንድሮ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሳካት የሠራው ሥራ እና ያመጣው ውጤት አበረታች መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በኮርፖሬሽኑ የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም እና የ2016 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ኮርፖሬሽኑ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸው÷ ያሣየውን ጥንካሬም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከሚያመርታቸው ምርቶች በተጨማሪ የመለዋወጫ ምርት እጥረቶችን ለመቅረፍ ምርቶቹን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
ኮርፖሬሽኑ የዕቅዱን ከእጥፍ በላይ ፈጽሟል ሲሉ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ኃ/ማርያም መናገራቸውን የመከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡
የአመራሩና አባሉ ቅንጅታዊ ሥራ እንዲሁም መከላከያ ሚኒስቴር ለኮርፖሬሽኑ የሰጠው ትኩረት ለስኬቱ ምንጭ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡