የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ከ132 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ለ2015 የአረንጓዴ ዐሻራና ለክረምት የበጎ አድራጎት ሥራዎች ከ132 ሚሊየን ብር በላይ መመደቡን ገለጸ፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም ወደብና ተርሚናል ባለባቸው አካባቢዎች ከ30 ሺህ በላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ችግኞች እንደሚተከሉ ተገልጿል፡፡
ከአረንጓዴ ዐሻራው ጎን ለጎንም የማኅበራዊ ድጋፍ ሥራዎች እንደሚሠሩ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ምህረተአብ ተክሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም÷ ለአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት፣ ለቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርት ቤቶች ግንባታ እንዲሁም ለትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ከ132 ሚሊየን ብር በላይ መመደቡን አንስተዋል፡፡
በ20 ሚሊየን ብር ወጪ ቅድመ መደበኛ ት/ቤት ለመገንባት በድሬዳዋ ከተማ ገዳንሳር ቀበሌ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ጠቁመው÷ ከሦስት ወራት በኋላ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡
የቅድመ መደበኛ ትምሕርት ቤት ግንባታው በገጠር ለሚኖሩ ሕጻናት የትምህርት ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምሕርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉካ መሐመድ ተናግረዋል፡፡
ሎጅስቲክሱ ቀደምሲል ሰባት ትምሕርት ቤቶችን አስገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተሾመ ኃይሉ