ፕሬዚዳንት ሩቶ በሱዳን አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በሱዳን አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት በትናንትናው እለት ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።
የኬንያ ፓርላማ እንዳስታወቀው÷ ከነበራቸው ውይይት በኋላ ፕሬዚዳንቱ በሱዳን ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚሰሩ ባላደርሻ አካላት ጥረታቸው ውጤት እንዲያመጣ በትብብር መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በሱዳን ግጭት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት የሚሰሩ ከሆነ በሱዳን የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ እርዳታ እንዲያገኙ ስደተኞች ጥበቃ እንዲደረገላቸው እንዲሁም በሱዳን ንግግር እንዲጀመር ተፅዕኖ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
ይህም በሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መሰረት ይጥላል ማለታቸውን ከኬንያ ፓርላማ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ፕሬዚዳንት ሩቶ ከጄኔራል አብድል ፈታህ አልቡርሃን በተጨማሪ ከቻዱ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ጋር የተወያዩ ሲሆን÷ የሱዳን ግጭት እንዲረግብ እና የሱዳን ስደተኞችን ለሚያስተናግዱ ሀገራት ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡