በአምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራ ልዑክ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው እቅድ ላይ ለመሳተፍ ድሬዳዋ ገባ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች እና ስራተኞች ልዑክ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው እቅድ ላይ ለመሳተፍ ድሬዳዋ ገብቷል፡፡
ልዑኩ በሐረሪ ክልል እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኞችን ለመትከል ድሬዳዋ ከተማ መግባቱ ተገልጿል፡፡
ልዑኩ ድሬዳዋ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐርቢ ቡሕ እና ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል እንዳደረጉለት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በክልሉ በሚካሄደው ታሪካዊው የአንድ ጀንበር የ500 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የክልሉ ነዋሪዎች አሻራውቸን በማኖር ታሪክ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አብዱልሃኪም ኡመር በበኩላቸው÷ በክልሉ የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ ዘመቻ ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በነገው ዕለት በመላው ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር የ500 ሚሊየን ችግኞች ተከላ እንደሚካሄድ ይታወቃል።