በድሬዳዋ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፣ የፕላንና ልማት ሚኒስተር ፍፁም አሰፋ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ብኽን እንዲሁም ከፍተኛ የፌዴራልና ክልል ባለስልጣናት አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የሠላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም ÷ በአስተዳደሩ የተጀመረው አረንጓዴ ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ ፥ የሚተከሉት ችግኞች ከደን ልማት ባለፈ ለምግብነት እንዲውሉ በማሰብ አስተዳደሩ በማዘጋጀቱ አመስግነዋል፡፡
በአስተዳደሩ በሁለተኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር 200 ሚሊየን ችግኞች ለመትከል ዕቅድ መያዙን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡኽ ገልፀዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 800 ሺው በዛሬው በአንድ ጀንበር 500 ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተተከሉ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
ይህም በአስተዳደሩ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ አስቻይነት እንደሚፈጥር ነው የጠቆሙት።
በአስተዳደሩ በመጀመሪያው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከተተከሉት ችግኞች መካከል ሰባ በመቶው ፀድቀዋል ብለዋል።
ዛሬ እየተተከሉ ያሉት ችግኞች የአየር ንብረት መሠረት አድርገው የተዘጋጁ ናቸው ያሉት ምክትል ከንቲባው ፥ ለዚህም ሞዴል ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውንም ነው ያነሱት።
የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ለማጠናከር በስጦታ 100 ሺህ ችግኞች አስተዳደሩ እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ለአጎራባች ምስራቅና ምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች እና ሱማሌ ክልል ሲቲ ዞን ተጨማሪ 100 ሺህ ችግኝ እንደሚበረከትም ነው የተነገረው።
ችግኞቹ በድሬደዋ አስተዳደር የአከባቢ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን የተዘጋጁ ሲሆኑ፥ ችግኞቹን በደን ዛፍ፣ በፍራፍሬ እና በከተማ ውበት ዘርፍ ለይቶ አዘጋጅቷቸዋል።
ከዘጠኝ የከተማና ከ38 የገጠር ቀበሌዎችም ችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ቀጥሎ እየተካሄደ ነው።
በእዮናዳብ አንዱዓለም