የአንድ ጀምበር ዘመቻ በራሱ አንድ ስኬት አንድ ግብ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢሲ) የዛሬው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በራሱ አንድ ስኬት አንድ ግብ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ፥ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ የዛሬው ቀን ኢትዮጵያን ፀጋ በማልበስ የሚታወስና ትልቅ ታሪክ እየተሰራበት ያለ ቀን ነው፡፡
“500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ሀገራዊ ፕሮግራም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን መትከል እዚሁ አካባቢ ብቻ የምንመለከተው ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድር በሁሉም ማዕዘናት በአሁኑ ሰዓት ይሄንን ሀገራዊ አጀንዳ ለማሳካት ሁሉም እየተሳተፈ ታሪክ እየሰራ ነው” ብለዋል፡፡
እኛም የፕሮግራሙ አጋሮች፣ ባለቤቶችና ተዋናዮች ሆነን እዚህ ተገኝተናል ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን÷ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ መትከል በራሱ ኢትዮጵያን በማልበስ ለነገ ትውልድ የተመቸ ሁኔታ ለመፍጠር ትልቅ ቁም ነገር መሆኑን አንስተዋል።
“በተጨማሪም ባለፉት አመታት ካሳካነው በላይ ክብረወሰኑን ለማሻሻል የይቻላል ውጤትን የምናሳይበት እለት ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
የመርሐ ግብሩ ትርጉም የእኛን የመሥራት አቅም የበለጠ ያነሳሳል፥ ለመጪው ዘመንም የተሻለ እንድንዘጋጅ እንዲሁም የዓለም ክብረወሰን የምንመራበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዓለም እየተፈተነች ካለበት አንዱ የአየር መዛባት መሆኑን ጠቅሰው÷ሀገርን ለመታደግ፣ ቀድሞ ወደነበረችውና ወደተሻለ ለማምጣት እንዲሁም ለዓለም ተምሳሌት ለመሆን ዛሬ ኢትዮጵያ ተሰልፋለች ብለዋል፡፡
በየሻምበል ምሕረት